ራስ አሉላ አባ ነጋ
“ከአሥመራ ወደ ምፅዋ ለሚወርድ መንገደኛ ምፅዋ ከመድረሱ ሃያ ኪሎ ሜትር ያህል ሲቀረው፥ ተድአሊ የተባለችውን ቀበሌ ያገኛል። ገና ከጊንዳዕ በታች የሚገኘውን ገደላ ገደል ወርዶ የዳማስን ሜዳ እንዳለፈ የሚጋረፈው የቆላ ሐሩር ይቀበለዋል። …ከሜድትራኒያን አከባቢ የሚነሣው የክረምት ጊዜ በቀይ ባሕር አካባቢ ያሉትን አገሮች ከልሎ በሚወስድበት ወቅት ቃጠሎውና ደረቁ አከባቢ ወደ ለምለምነት ስለሚለወጥ ከጊንዳዕ ጀምሮ እስከ ምፅዋ ያለው ወረዳም ከጥቅምት እስከ ሚያዚያ መጨረሻ ድረስ የሚታይበት ውበት፥ የሚገኝበት የመሬት ፍሬና የአየር ለውጥ የማይጠገብ ነው።ራስ አሉላም ከጊንዳዕ ወደ ሰሐጢ የወረዱት በጥር አጋማሽ ላይ ነበር። የአየሩ ጠባይ አልፎ አልፎ ዝናብ የሚጥል መሬቱ በልምላሜ የተሸፈነ ነበር። …
ራስ አሉላ፥ በተፈጥሮአቸው ከወረሱት ጸጋ የጦር ስልት ሲያወጡ ወይም ጦርነት ለመግጠም ሲያስቡ የአየር ጠባይንም በቅድሚያ ለማወቅ የሚያደርጉት ጥረት ነው። ሠራዊታቸው በሐሩር፥ በጨለማ፥ በወባ፥ በኃይለኛ ዝናብ ጎርፍና ጉም እንዳይጠመድባቸው እጅግ ይጠነቀቁ ነበር። ……ራስ አሉላ ከንጋቱ ላይ ሰሐጢ አጠገብ ደርሰው የወታደራቸውን አሰላለፍ በዝርዝር ተመለከቱ። … ፀሐይ ስትወጣ ከጀርባቸው እንድትሆን አደረጉና ጦርነቱን ጀመሩ። … የመድፍና የጠመንጃው ተኩስ ቀረና ውጊያ በጨበጣ ሆነ። ራሳቸው ራስ አሉላ ከፈረሳቸው ወርደው እንደ ተራ ወታደር በተድአሊ ወንዝና ዳገት እየዘለሉ ከጠላት ጦር ጋር ተደባለቁ። … ጉራዕ ላይ በግብፅ ኩፊት ላይ በድርቡሹ አንገት ላይ በደም ያጠቡትን ጎራዴያቸውን መዘዙና የጣልያኑ ጦር መከላከያ ለመሥራት ሲጣደፍበት ወደነበረው ቁብታ ወጥተው ለሸለሹት። …
[…አቀንቃኝ…] ኪዳኔ መብራቱም፥
“ጎራው ተማሙቋል መሬት ተደባልቋል፤
ነጩ ክምር ፈርሶ ምስቅልቅሉ ወጥቷል።
…ሚስትህ ምነው ባየች በሰማች እናትህ፤
በአሉላ ጎራዴ ሲበጠስ አንገትህ።
የነማን አገር ነው ብለው ሳይጠይቁ፤
አገር የደፈሩ እነሆ ወደቁ።
ምነው በጠየቁ የግብፅን ወታደር፤
ምነው በጠየቁት የድርቡሽ ወታደር፤
እንደማይደፈር ያባነጋ መንደር።”እያለ አቅራራ።”
አሉላ አባ ነጋ | ከማሞ ውድነህ | 1979 ዓ.ም ታተመ | ገጽ 237-241
No comments:
Post a Comment