Saturday, May 5, 2012
ውውውው........ውሸትን እንግታ!
የሰው ልጅ ውሸትን ለተለያየ ምክንያትና አላማ ይጠቀምበታል። አብዛኞቻችን ከሰወች በልጦ ለመታየት ስንል እንዋሻለን።ወይ ደግሞ ሰወችን ለመወንጀል ።
ውሸትን ባስፈለገህ ሰአትና ጊዜ ልትጠቀመው ትችላለህ።ከእውነታ የተሻለ ቦታ ሲኖረው ትመለከትና “ብዋሽ ያዋጣኛል” በሚል ግልፍ ስሜት አስበህበትም ይሁን ሳታስብበት ትዋሻለህ።ነገር ግን ውሸት ስትገባበት እንጂ ለመውጣት ከባድ ነው።እናም ስትዋሽ እንዴት፣ወዴት፣ከየት፣ለምን የሚሉትን ጥያቄወች ማስተናገድ ያስጠላሀል።የውሸት ወሬህን ሳትጨርስ ህሊናህ መድማት ይጀምራል።“ከዚህ በኃላ ብዋሽ ከምላሴ ፀጉር ይነቀል” ትለዋለህ ለምላስህ። በሌላ ጊዜ እንዲህ አይነት መዘዝ ውስጥ እንዳይከትህ ለማስጠንቀቅ ያህል።ነገር ግን ለአሁኑ እራስክን ለማረጋጋት ብለህ ምላስክን እየዋሸኸው እንጂ በሌላ ጊዜ መዋሸትህ እንደማይቀር ልብህ ሹክ ይልሀል::ላብህ እየመጣም ቢሆን ወሬህን ትጨርሳልህ።ነገር ግን ላብህ ሊመጣ አይገባም ነበር።መሪህ ሲዋሹ አላየሀቸውም? ፀጉር የለለውን እራሳቸውን ያካሉ አንጂ ላባቸው አይመጣም።እንዲህ አይነቱ ጥበብ የሚመጣው ደግሞ ብዙ ከመዋሸት ነው።
ይህን ሁሉ የተንዘባዘብኩት እዚህ ባህር ዳር ውስጥ እኔ በማስተምርበት የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ የሚማሩ ሁለት ህፃናት ሲያወሩ የሰማሁት ነገር ስላስደነቀኝ ነው።እንደነዚህ አይነት ውሸታሞች በህይወቴ አጋጥሞኝ አያውቅም።አይደለም የአራተኛ ክፍል ተማሪወች የአራተኛ ክፍል አስተማሪም እንዲህ አይነት ውሸት ይዋሻል ብሎ ማሰብ ይከብዳል።
የማስተምራቸው ስዕል ስለሆነ እያወሩ፣ እየተጫወቱ እንዲማሩ እፈቅድላቸዋለሁ።እናም ትናንትና ተራራ እንዲስሉ አዘዝኳቸውና እየዞርኩ የሚስሉትን ስዕል መቃኘት ጀመርኩ።ታዲያ በዚህ ሰአት ነበር ጀሮ የሚደፍን፣ ጭንቅላት የሚያዞር ውሸት የሰማሁት።
የሁለቱንም ልጆች ቤተሰቦች አውቃቸዋለሁ።የአንዱ አባቱ ግንበኛ ሲሆን ያንዱ ደግሞ አሳ አጥማጅ ነው።
ታዲያ የግንበኛው ልጅ፦ “አባቴ እኮ በጣም የታወቀና የሚደንቅ መሃንዲስ ነው። ማንኛውንም ነገር መስራት ይችላል።ራስ ዳሽንን ታውቀዋለህ?” ሲል የአሳ አጥማጁን ልጅ ጠየቀው።
“አዎ አውቀዋለሁ” ብሎ መለሰለት።
“እሱን የሰራው አባቴ ነው።” አለው ።
የአሳ አጥማጁም ልጅ አድናቆቱን ገለጸና በተራው “የኔም አባት እኮ በጣም ጎበዝ መርከበኛ ነው።ለምሳሌ ሞት ባህርን ታውቀዋለህ?” ብሎ ጠየቀው።
“አዎ ሲጠራ ሰምቻለሁ።” አለ የግንበኛው ልጅ።
“እየሁልህ እሱን የገደለው አባቴ ነው” አለው።
ይህን ስሰማ ለእናት ኢትዮጵያ አዘንኩላት።ይህን ትውልድ ይዛ እንዴት ነው ጉዞዋን የምትቀጥለው ስል እራሴን ጠየኩ።ይች ሀገራችን በስልጣኔ ፊት መርታ መርታ ደክሞት ወደ ኃላ እንደቀረች ይታወቃል። አሁን ግን አይደለም ወደ ኃላ መቅረት መሞቷ የማይቀር ነው።እናም ልጆቻችን በውሸት በሽታ ሳይጠቁብን ቀድመን እውነትን ከፖሊዮ ጋር እናስከትባቸው።
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
እዚህ ባህር ዳር ውስጥ እኔ በማስተምርበት ...ውሸትን እንግታ!
ReplyDelete